አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ የተባለ 200 ሚሊየን የሕክምና ቴስት ኪቶችን በዓመት የሚያመርት የቻይና ኩባንያ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰስ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከጉዋንዥሁ ወንድፎ ባዮቴክ ኩባንያ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመው ÷ይህም ኩባንያው በፍጥነት ወደ ሥራ ገብቶ ስራ እንዲጀምር ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና የቻይናውያን ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከ40 በላይ የቻይና ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው÷በዚህም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድልን መፍጠር ችለዋል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኩባንያው ተወካዮች በበኩላቸው÷ድርጅቱ በሁለት ምዕራፎች ሥራውን እንደሚያከናውን ገልጸው÷ በዚህም ከ15 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባም ወደ ሌሎቸ የአፍሪካ ሀገራት ለመላክ በእቅድ መያዙ ነው የተመላከተው፡፡
በፈረንጆቹ 1992 የተመሰረተ ው ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ ኩባንያ በጤናው ዘርፍ ላይ የተሰማራና ለ150 በላይ ሀገራት ምርቱን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡