Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢሬቻ ፈጣሪ ለፍጥረታት ላደረገው ሁሉ ምስጋና የሚቀርብበት የሰላምና የወንድማማችነት በዓል ነው – አባገዳዎች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ ፈጣሪ ለፍጥረታት ላደረገው ሁሉ ምስጋና የሚቀርብበት ፣ ሰላምና ወንድማማችነት የበለጠ የሚጠናከርብት በዓል መሆኑን አባገዳዎች ገለጹ።

የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን ÷ የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪ ዋቃ ምስጋናውን የሚያቀርብበት በዓልን ነው።

አባገዳዎች እንደሚሉት÷ኢሬቻ በክረምትና በጨለማ የነበረው አስቸጋሪ ወራት ማለፉንና በጸደይ ጸሃይ ስትወጣና ብርሃን ሲታይ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው ፡፡

አባገዳ ዳውድ ዓሊ÷ኢሬቻ የሚከበረው ፈጣሪ ለሰው ልጅ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና ለማቅረብ እና ወደ ፊት እንዲሆን ለሚፈለግ ነገር ለመማጸን ነው፤ የኦሮሞ ህዝብም ፈጣሪ የፈጠረውን ለምለም ሳርና አደይ አበባ ይዞ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጸሃፊ አባገዳ አብዱራዛቅ አህመድ በበኩላቸው÷የኦሮሞ ህዝብ ከባዱን የክረምት ወራት ያሳለፈውን ፈጣሪውን ወደ መልካ በመውረድ እንደሚያመሰግንና በንፁህ ልቦና ይቅርታን እንደሚጠይቅ አውስተዋል።

በዚህም የኢሬቻ በዓልን የሚታደም ማንኛውም ሰው ከቅርብ ሰው ጋር እንኳን ግጭት ከፈጠረ መጀመሪያ ከራሱም ሆነ ከሌላው ሰው ጋር መታረቅ አለበት ብለዋል።

ይቅርባይነትና መመሰጋገን በማህበረሰብ ውስጥ እንዲኖር “ቂም ቋጥሮ ኢሬቻ ቦታ አይኬድም” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢሬቻ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነትና የውበት የሚንጸባረቅበት መድረክ ነው ያሉት ደግሞ አባገዳ ደቻሳ ወዳጆ ናቸው።

ኢሬቻ የሰላም በዓል መሆኑን ከሚያመላክቱ ነገሮች ውስጥ የተጣላ፣ ግጭት ውስጥ የገባ ሰው እንዲታረቅና ሰላም እንዲሰፍን በሰው ልጆች መካከል ፍቅር እንዲሰፍን ማድረጉ ነው ብለዋል።

Exit mobile version