አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ትናንት ምሽት እስራኤል በኢራን የተተኮሱ ሚሳኤሎችን እንድታከሽፍ የጸረ- ባላስቲክ ሚሳኤል ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች፡፡
በፔንታጎን መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ፓትሪክ ራይደር÷ ወደ ቴል አቪቭ የተተኮሱ ባላስቲክ ሜሳኤሎችን ለማክሸፍ አሜሪካ ብዛት ያላቸው ፀረ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን አሰማርታ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡
ኢራን ቀደም ሲል 110 የባላስቲክ ሚሳኤሎችን እና 30 የመርከብ ሚሳኤሎችን ተኩሳ እንደነበር አስታውሰው÷ የአሁኑ ጥቃት ኢራን ከምንገዜውም በላይ በቁጥር በርከት ያሉ ሚሳኤሎች የተኮሰችበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስለ ኢራን ጥቃት ዝግጅት አሜሪካ ምንም አይነት እውቅና እንዳለነበራትም ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው÷ ኢራን ወደ እስራኤል የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ከጠዋት ጀምሮ በነጩ ቤተ መንግስት በተገነባው የሁኔታ መከታተያ ክፍል ውስጥ መማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ እስራኤል ባደረገችው የሚሳኤል መከላከል ድጋፍ ማድረጓንም አረጋግጠዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ኢራን 180 የሚጠጉ ሚሳኤሎች ወደ መተኮሷን የገለፀ ሲሆን ከተተኮሱት ውስጥ አብዛኛዎቹ ሚሳኤሎች በጸረ ባላስቲክ ሚሳኤል አማካኝነት ከሽፈዋል ብሏል፡፡
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን÷ ጥቃቱ የኢራንን ጥቅም እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው÷ ኢራን ከባድ ስህተት ፈፅማለች በማለት ጠቅሰው፤ ከበደ ያለ የአፀፋ ምላሽ እንደሚጠብቃት ዝተዋል፡፡