አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዓለም ሎሬት ጋቢሳ እጀታ(ፕ/ር) ከተመራ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ከመጡ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ከአሜሪካ ጋር በትብብር መስራት በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚህም ሁለቱ ወገኖች በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በምርጥ ዘር አቅርቦት እና ስርጭት እንዲሁም በእንስሳት ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ÷ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበውን አበረታች ለውጥ ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ፍላጎት ገልፀዋል፡፡
ጋቢሳ እጀታ (ፕ/ር)በበኩላቸው÷የግብርና ስራ ቁርጠኝነት እና መልካም አስተዳደር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው ÷ምርጥ ዘር አመራረት፣ አቅርቦት እና ስርጭት እንዲሁም የእንስሳት ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት እና ተራድዖ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም ጋቢሳ(ፕ/ር) ማረጋገጣቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡