የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ደህንነትና ስራዎች ላይ ያተኮረ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

By Meseret Awoke

October 01, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2024 ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ደህንነት እና ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ በሞሮኮ ማራኬሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጉባኤው፥ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂን ለአስተማማኝ እና ቀልጣፋ ስራዎች በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በጉባዔው የታደሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ልምዳቸውን አጋርተዋል።

በዚህም በአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን ቡድን የመምራት ልምድና ዕውቀትን አካፍለዋል ነው የተባለው፡፡

በዚህም በወሳኝ የአቪዬሽን ጉዳዮች ላይ የስራ ቅልጥፍና እንዲኖር የፈጠራና የቴክኖሎጂ በጎ ሚና፣ ዘላቂ ግቦችን በመደገፍ እንዲሁም የደንበኞችን ልምድ በማጎልበት ላይ ግንዛቤ አስጨብጠዋል ተብሏል፡፡

ጉባኤው እስከ ፊታችን ሐሙስ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፥ ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን፣ የደህንነት ባህልን እና አፈፃፀምን ለማሻሻል መረጃዎችን እና ፈጠራዎችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መረጃ አመላክቷል።