አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለማስተካከል ሕግ የማስከበር ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በክልሉ እየተከናወነ ያለውን ሕግ የማስከበር ርምጃ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የክልሉ መንግሥት የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ተደጋጋሚ የሰላም ጥረቶችን ማድረጉን ያስታወሱት መንገሻ (ዶ/ር)÷ መንግሥት ሰፊ የሰላም አማራጮችን ዘርግቶ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ቢሞክርም ምላሹ ግን በሚፈለገው መንገድ አልሆነም ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም መንግሥት ሳይወድ በግድ ሕግ ለማስከበር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መገደዱን ገልጸው÷ መከላከያ እና የክልሉ መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ተግባር በቅንጅት እያከናወኑ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እና ግጭቱን ለመቋጨት በርካታ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ውይይቶች እና ምክክሮች ተካሂደው እንደነበር ጠቅሰው÷ የታጠቁ ኃይሎች ምላሽ ግን የሕዝብን ስቃይ እና መከራ አባብሷል ብለዋል፡፡
ይባስ ብሎ የታጠቁት ኃይሎች ከሀገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ አስታውቀዋል፤ ጥምረታቸውም በመታዘዝ፣ በሎጀስቲክስ እና በወታደር ድጋፍ እንደተጀመረ መንግሥት ደርሶበታል ነው ያሉት ኃላፊው።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሕግ የማስከበር ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው÷ ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ አሳስበዋል።
ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቀርብዋል፡፡