Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጪ የመሸፈን ድርሻውን ወደ 60 በመቶ ለማድረስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 20 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን ወጪ የመሸፈን ድርሻ 60 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የክረምት የገቢ አሰባሰብ የንቅናቄ ስራዎችንና በዘርፉ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን የሚገመግም መድረክ በቡታጅራ አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አሊ ከድር በወቅቱ እንደገለጹት÷ የህብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት በአግባቡ ገቢ ለመሠብሰብ እየሰራ ነው።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ክልላዊ ገቢውን 20 ቢሊየን ብር በማድረስ ከ50 በመቶ በታች የነበረዉን የክልሉን ወጪ የመሸፈን ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ገቢውን በማሳደግ ለክልሉ አጠቃላይ ምርት ያለውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

ይህንን ግብ ለማሳካት የታክስ ህግ ተገዥነትን በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ፣ ህገወጥ ግብር ከፋዮችን ወደ ህጋዊ ሥርዓት ማምጣትና ያለደረሰኝ ግብይት ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

የታክስ አስተዳደሩን ሥርዓት ማዘመን፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግና በደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በሙከራ ደረጃ የተጀመረዉን የኦንላይን ክፍያ ማስፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ግዴታቸውን በማይወጡ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

Exit mobile version