የሀገር ውስጥ ዜና

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማስፋፊያ ግንባታ በ300 ሚሊየን ዶላር ሊከናወን ነው

By Feven Bishaw

October 01, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ የማስፋፊያ ግንባታ በ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማከናወን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ቱፋ÷ በመጀመሪያው ዙር የተናከነወነው የኢንዱስትሪ ፓርኩ አካል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች ተይዟል ብለዋል።

ዘንድሮ ግንባታው የሚጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከ120 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን ጠቁመው በ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚከናዋን ገልፀዋል፡፡

ግንባታውን ከቻይና ሁናን ግዛት የመጡ ባለሀብቶች ለመጀመር መግባባት ላይ መደረሱንና ግንባታውን ለመጀመር የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ትላልቅ ማሽነሪዎች የሚመረቱበትና ሀገሪቷ ለዚህ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት ባለፈ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑንና ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡