አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር በሰላምና ልማት ግንባታ ላይ እያደረጉት ያለው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ አሳሰቡ።
ርዕሰ መስተዳድሯ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የተለያዩ ድርጅቶች በክልሉ የሚያከናውኑት የሰላምና ልማት ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ በርካታ ሀብት እንዳለው ጠቅሰው፤ በተገቢው መንገድ ለምቶ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከመንግስት ጋር በጋራ ቢሰሩ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይቻላል ብለዋል።
በቀጣይም ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በትብብር ይሰራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የስደኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ አንድሪው ቦጎሪ÷ ድርጅቱ ከጋምቤላ ክልል ጋር በተለያዩ ዘርፎች ሲሰራ መቆየቱን አንስተው፤ የልማት ትብብሩና ድጋፉ ይጠናከራል ብለዋል።