የሀገር ውስጥ ዜና

በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የፐርፐዝ ብላክ የቦርድ አስፈጻሚዎች ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

By Shambel Mihret

October 01, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማታለል ሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የፐርፐዝ ብላክ የቦርድ አስፈጻሚን ጨምሮ በአራት ግለሰቦች ላይ ክስ የመመስረቻያ ጊዜ ተፈቅዷል፡፡

የክስ መመስረቻያ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

በዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቻያ ጊዜ የተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች 1ኛ የፐርፐዝ ብላክ የቦርድ አባልና የቦርድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ ብርሀኑ፣ 2ኛ የድርጅቱ ኦፕሬሽን ኦፊሰር ኤፋታት (ሶፍያ) ነጋሽ፣ 3ኛ የድርጅቱ ሰራተኛ ብሩክ በነበሩ ደስታ እና የገበሬ ቲቪ (TV) ባለሙያ ዋሲሁን ዋጋ አሰፋ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ በ100 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ባለ 3 መኝታ መኖሪያ ቤት በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ በማስተዋወቅ ሰዎች ቤት ለመግዛት በሄዱበት ጊዜ “መጀመሪያ ገንዘቡን አስገቡና ውሉን ትመለከታላችሁ “በማለት ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር ሆነው አሳሳች ቃላት በመጠቀም፣ ሰዎች ገንዘቡን ካስገቡ በኋላ የአክሲዮን ግዥ ውል እንዲፈርሙ አድርገዋል ተብሏል፡፡

የግንባታ ቦታ ባልተረከቡበት ሁኔታም 2 ቢሊየን 234 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ ቤቱን ሰርተው ሳያስረክቡ በመቅረት እና ግማሹን ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ በማድረግ በሕዝብ ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሎ በአዲስ አበባ ፖሊስ በኩል በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የምርመራ ማጣሪያ ስራ ሲከናወንባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ፖሊስም የምርመራ ማጣሪያ ስራውን ማጠናቀቁንና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለችሎቱ አስታውቋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጾ÷ መዝገቡን ተመልክቶ ለመወሰን እንዲያስችለው በሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት የ15 ቀን ክስ መመስረቺያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ ደንበኞቻቸው ተጨማሪ ጊዜ በእስር ሊቆዩ እንደማይገባ ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎትም በዛሬው ቀጠሮ የክስ መመስረቺያ ጊዜ መፍቀድ ተገቢ መሆኑን በማመን ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ መመስረቺያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ