የሀገር ውስጥ ዜና

በታይላንድ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ20 በላይ ህጻናት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ

By Meseret Awoke

October 01, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በታይላንድ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ20 በላይ ህጻናት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገልጿል፡፡

ከታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ወጣ ብሎ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተጋጭቶ በእሳት መያያዙም ነው የተጠቆመው፡፡

አደጋው በተከሰተበት ወቅት 16 ህጻናት እና ሦስት መምህራን ራሳቸውን ማዳናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ 22 ተማሪዎች እና ሦስት መምህራን ግን የአደጋው ሰለባ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተገልጿል።

እንደ ሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ፤ በአውቶቡሱ ውስጥ አሥር አስከሬን ተገኝቷል።

አውቶቡሱ ሙሉ በሙሉ በእሳት መውደሙን የተገለጸ ሲሆን፥ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአውቶቡሱ ግለት ምክንያት ወደ ውስጥ መግባት አልቻሉም ተብሏል።

በሰሜናዊው የኡታይ ታኒ ግዛት ከትምህርት ቤት የመስክ ጉብኝት ሲመለሱ ከነበሩት ሦስቱ አውቶቡሶች አንዱ አደጋው እንደደረሰበት ቢቢሲ ዘግቧል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሱሪያሄ ጁዋንግሩንጉራንግኪት፥ አደጋው የተከሰተው አውቶብሱ ከሚጠቀመው የጋዝ ዓይነት ጋር ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ መሰል የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሸከርካሪዎች የሚጠቀሙት ጋዝ ሊለይ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡