Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ለአረጋውያን መብት መከበር ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረጋውያን መብት እንዲከበርና የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ አሳሰቡ፡፡

ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን ለ33ኛ ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ “ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን” በሚል መሪ ሐሳብ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ አረጋውያንን በክብር መያዝና በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡

አረጋውያን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ ጌታቸው በዳኔ በበኩላቸው÷ የአረጋውያን መብቶች እንዲከበሩ የንቅናቄ ሥራ ከመሥራት ባሻገር የማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ትውልዱ አባቶቹን የማክበርና የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳላበት ያስገነዘቡት ደግሞ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አባ ሙዳ አበበ ናቸው፡፡

ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን የአረጋውያንን መብት ለሕብረተሰቡ ከማስገንዘብ ባሻገር መብታቸው በሥራ ላይ እንዲውልና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ለማስቻል በየዓመቱ ይከበራል፡፡

 

Exit mobile version