አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ሄዝቦላህን ለማጥቃት የአጭር ጊዜ ተልዕኮ በመያዝ እግረኛ ሰራዊቷን ወደ ሊባኖስ ማስገባቷን አስታወቀች፡፡
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የተገደበና ዒላማ ያለው የምድር ላይ ተልዕኮ ብላ የገለጸችውን በእግረኛ ሰራዊቷ የሚከናወን ዕቅዷን ይፋ አድርጋ በሂዝቦላህ ላይ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን ገልጻለች።
እንደ የእስራኤል መከላከያ ሃይል፥ ተልዕኮው ሂዝቦላህ በኢራን ድጋፍ እየተደረገለት በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ማህበረሰቦች ላይ የሚፈጥረውን ስጋት ለመቀነስ በማለም እንደሆነ ጠቅሷል።
በዚህም ሂዝቦላህ ጥቃት ለማድረስ ይጠቀምባቸዋል የተባሉ መሰረተ ልማቶች የእግረኛ ሰራዊቱ ዒላማ እንደሆኑ አመልክቷል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት፥ በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ለሚገኙ ወታደሮች እስራኤል ሂዝቦላህን በአየር፣ በባህር እና በምድር ሃይሎች በመጠቀም ጥቃት ለማድረስ መዘጋጀቷን ቀደም ሲሉ አመላካች መረጃ መስጠታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
በአንጻሩ የሂዝቦላህ ምክትል መሪ፥ ቡድኑ በሊባኖስ ውስጥ ለሚደረገው ማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የሊባኖስ ባለስልጣናት ባለፉት ሁለት ሣምንታት ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና በአሁኑ ወቅት እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አለብን ሲሉ ተናግረዋ ነው የተባለው፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ደግሞ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቁ ሲሆን፥ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች ሁኔታውን በእጅጉ እንደሚያባብሰው አስገንዝቧል።