አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለውጡ ወዲህ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ያካሄድነው የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት ጥሏል ሲሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት በአመራርና በሰው ኃይል የተጠናከሩ፣ አቅማቸው በቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ በደህንነት መሰረታዊና አንኳር ክህሎቶች የፈረጠሙ እንዲሆኑ ሰፊ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተቋማቱ በዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ የታነፁ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ በትኩረት መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡
በውጤቱም ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ፣ ወገንተኝነታቸው ለህግ ብቻ የሆኑ፣ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ላይ ፈፅሞ ክፉ እንዳያስቡ የሚያደርጉ፣ ለሀገር ጋሻ እና ጥላ የሆኑ ተቋማት ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር፣ ግጭት ቀስቃሽ አስተሳሰቦችንና ተግባራትን የሚጠየፍ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል ማዳበርና ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በአባቶቻችን ደምና አጥንት ታፍራና ተከብራ የመኖሯ እውነታ ከቶ እንዳይደፈር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም ተቋማዊ አቅምን እና የሕዝቡን ድጋፍ ይበልጥ እያጎለበቱ መሄድ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡