አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማኅበራዊ ጥበቃን በገንዘብ ለመደገፍ ጥሩ ዕድል መፍጠሩን የዓለም ባንክ ተወካዮች ገለጹ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎች ከዓለም ባንክ ተወካዮች ጋር በማህበራዊ ጥበቃ የፖሊሲ ማሻሻዎች፣ ቀጣይ ስለሚደረገው የማሕበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስና የከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችን በቅንጅት መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ዓለም ባንክ የማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች ላይ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመድረስና በቅንጅት ከመስራት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከማህበራዊ ጥበቃ ምዝገባ ሂደት እስከ ፖሊሲ ማሻሻል ድረስ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡
ለዚህም የዓለም ባንክን ትብብር አስፈላጊ ነው መባሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የዓለም ባንክ ተወካዮች በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማኅበራዊ ጥበቃን ጨምሮ ሌሎች የልማትና የትብብር መስኮች ላይ በቅንጅት ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በዘርፉ ለሚሰራው ስራ የዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።