የሀገር ውስጥ ዜና

የግሸን ማርያምን የንግሥ በዓልን ለማክበር እንግዶች እየገቡ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

September 30, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን የሚከበረውን የግሸን ማርያም የንግሥ በዓል ለማክበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች እና ቱሪስቶች ወደ ቦታው እየገቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አስያ ኢሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የግሸን ማርያምን የንግሥ በዓል በድምቀት ለማክበር የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች እና ቱሪስቶች በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡

ምዕመናን ወደ አካባቢው ሲመጡ በአግባቡ ተስተናግደው እንዲመለሱ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን እና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡

በዋናነት ከበዓሉ አክባሪዎች በተጨማሪ ቱሪስቶችም ወደ ግሸን ደብረ-ከርቤ እንደሚመጡ ጠቁመው፤ ይህም ለአካባቢው ማሕበረሰብ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙም ማሕበረሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በሰሎሞን ይታየው