አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳይ ናሽናል ራሊ ፓርቲ የረጅም ጊዜ መሪ የሆኑት ማሪን ሌፔ እና አባላቶቻቸው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ገንዘብን ያለ አግባብ ጥቅም ላይ በማዋል ውንጀላ ቀረበባቸው።
ከማሪን ሌፔ በተጨማሪ ከ20 በላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ውንጀላ ቀርቦባቸዋል ነው የተባለው፡፡
የፓርቲው አባላት ክፍያ ከከፈላቸው የአውሮፓ ፓርላማ ይልቅ ከፓርቲው ጋር የሚሰሩ ረዳቶችን በመቅጠራቸው መከሰሳቸው የተገለጸ ሲሆን ፓርቲው የቀረበበትን ውንጀላ ውድቅ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
የፓርቲው ቃል አቀባይ ሎረንት ጃኮቤሊ ከአውሮፓ ህብረት ገንዘብ የሚመዘበርበት ምንም አይነት አሰራር እንደሌለ ገልፀው÷ በአውሮፓ ፓርላማ የሚሰራ እና ከፓርቲው ጋር ግንኙነት ያለው ሰው መቀጠሩን ፓርቲው ያጣራል ብለዋል፡፡
የፈረንሳዩ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪ የሆኑት ማሪን ሌፔ በተወነጀሉበት ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኘኙ በገንዘብ እና በእስራት ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ለ10 ዓመታት ያህል በፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አይሳተፉም የተባለ ሲሆን ይህም የፕሬዚዳንትነት ህልማቸውን ሊያጨልም እንደሚችል መመላከቱን ቢቢሲ ዘግቧል።