አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ70 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ስምምነት ከዓለም ባንክ ጋር ተፈራርማለች፡፡
ገንዘቡ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ሲሆን በኢትዮጵያ የአስተዳደር ስራዎችን ለማቀላጠፍና ለማዘመን ሥራ እንደሚውል ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ የመንግስትን የፋይናንስና የሰው ሃይል የማሰባሰብ እንዲሁም የማስተዳደር አቅሙን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የሰው ሃብት አስተዳደር አሰራርን ማዘመን፣ በብቃት ላይ የተመሰረተ የቅጥርና የአመራር ሂደቶችን ማጎልበት እና የመንግስት ሰራተኛን አቅም የመገንባት ስራዎች በማከናወን የመንግስት አስተዳደርን የማኔጅመንት አቅሞችን ለማሻሻል ይሰራል ተብሏል።
በመቀጠልም የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ለማሻሻል በፕሮጀክቱ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፥ ግብር በታዛዥነትና በፍላጎት እንዲከፈል ለማድረግ እንዲሁም ክፍተቶችን መሙላት ላይ አጽንኦት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡
በሦስተኛ ደረጃም የህዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ዲጂታል መፍትሄዎችን ማስፋት፣ በዚህም ውስጥ ያሉ ወሳኝ የሂደት ጉድለቶችን በመፍታት፣ የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም እንዲሻሻል ድጋፍ በማድረግ የሂሳብ አያያዝ እና የግዥ ሙያዊ ብቃት ላይ ድጋፍ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም መፈረማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡