የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ከአጭበርባሪዎች እንዲጠነቀቁ አሳሰበ

By Shambel Mihret

September 30, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አጭበርባሪዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከሚፈጽሙት የገንዘብ እና የመረጃ ስርቆት ደንበኞቹ እንዲጠነቀቁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሳሰበ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም እና አሳሳች ማስታወቂያዎችን በማሰራጨት የማጭበርበር ሙከራዎች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን ባንኩ አስገንዝቧል፡፡

በዚህም አጭበርባሪዎች ‘የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መጠይቅ በመሙላት የገንዘብ ስጦታ ታገኛላችሁ’ የሚል አሳሳች መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑን ነው ባንኩ የጠቀሰው፡፡

አጭበርባሪዎች የባንኩን ስም እና ዝና በመጠቀም ሕገ-ወጥ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ከሚያደርጉት ሙከራ ራስን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡

ደንበኞች መሰል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ትክክለኛነቱን ሳያረጋግጡ ምንም ዓይነት ርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ ወይም በ951 የባንኩ የደንበኞች ጥሪ ማዕከል በመደወል ስለሁኔታው እንዲያጣሩ መክሯል፡፡

በተጨማሪም የባንኩን ትክክለኛ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ብቻ በመከተል ደንበኞች ራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡