አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለዓለም አቀፍ ትብብር የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አረጋገጡ፡፡
እየተከበረ በሚገኘው የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ 75ኛ ዓመት ላይ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር÷ ቻይና ባለፉት አሥርት ዓመታት ያስመዘገበችውን ጉልህ ስኬቶች አብራርተዋል፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የረጅም ጊዜ ማኅበራዊ መረጋጋትን በማስፈን ረገድ የነበረውን ሚና አንስተዋል፡፡
ለቻይና ልማት ድጋፍ ላደረጉ ዓለም አቀፍ ወዳጆች፣ ለሀገሪቱ መመስረት እና ብልጽግና አስተዋጽዖ ላበረከቱ የቀድሞ መሪዎች እና ጀግኖችም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በሁሉም ሥራዎች ሕዝብን ማስቀደምና ሰላማዊ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ÷ ቻይና ለዓለም አቀፍ ትብብር እና የአሥተዳደር ማሻሻያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ እና ለሰው ልጅ ብሩህ ተስፋን ለመገንባት የጋራ ርብርብ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
በአፈወርቅ እያዩ