Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከተማ አስተዳደሩ ለክልሎች ኮሪደር ልማት ውጤታማነት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል – አቶ ጃንጥራር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ከተሞች ከአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ልምድ ወስደው ለነዋሪዎች ምቹና ያማሩ እንዲሆኑ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።

አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በደሴ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት አቶ ጃንጥራር እንደገለፁት÷ አዲስ አበባ ከተማን በኮሪደር ልማት ውብና ለነዋሪዎች የተመቸች ማድረግ ተችሏል።

የክልል ከተሞችም ከዚሁ ልምድ በመውሰድ በኮሪደር ልማት ማስዋብና ምቹ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው÷ ልምድ ለማካፈልና ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በደሴ ከተማም ቀደም ሲል ተጀምሮ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በማጠናከርና በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

በተለይም ህብረተሰቡን በማስተባበር ሌት ተቀን በመስራት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው÷ በከተማው ህብረተሰቡን በማስተባበር በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

 

Exit mobile version