Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሐረሪ ክልል የኮሪደር ልማት ሥራን በገጠር ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በገጠር ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሐረር ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶችን በወረዳ ደረጃ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከወረዳ አመራሮች ጋር በመከሩበት ወቅት÷ በሐረር ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የኮሪደር ልማቱን በወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ለመንገድ ሥራ 1 ቢሊየን የሚደርስ ብር መመደቡን ጠቅሰው÷ በከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶች ማስፋፊያ እንዲሁም በገጠር ወረዳዎች አዳዲስ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አንስተዋል።

የኮሪደር ልማቱ በተለይ በገጠር ወረዳዎች ሰፋፊ፣ ፅዱ እና ምቹ የእግረኛ እና መኪና መንገዶች እንዲኖሩ በማስቻል የሚስተዋለውን የመንገድ ላይ ንግድና ፅዳት ችግር ስርዓት ለማስያዝ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

የኮሪደር ልማቱ በወረዳዎቹ በቀጣይ በሚከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል አመራሩ ሕገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ኦርዲን፤ በቀጣይ በከተማና ገጠር ወረዳዎች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን የክልሉ ካቢኔ አባላት በወረዳዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲያደርጉ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

Exit mobile version