አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር በሚያደርጋቸው ሦስተኛ እና አራተኛ የምድብ ጨዋታዎች ላይ የቀን እና የቦታ ለውጥ መደረጉ ተገለጸ፡፡
በጨዋታዎቹ ላይ የቦታ እና የቀን ሽግሽግ ማድረግ ያስፈለገው የኢትዮጵያ እና የጊኒ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ለካፍ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚሁ መሠረት ሦስተኛው የምድብ ጨዋታ ጊኒ የሜዳዋ ጨዋታን ለማድረግ ያስመዘገበችው ያሞሱክሩ የሚገኘው ስታድ ኮናን ባኒ ወደ አቢጃኑ ስታድ ደ ኢቢምፔ ተቀይሯል ተብሏል፡፡
የጨዋታው ቀንም ቀደም ብሎ ከተገለጸው ጊዜ በአንድ ቀን ተራዝሞ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ምሽት 1 ሠዓት ላይ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
እንዲሁም አራተኛው የምድብ ጨዋታ በተመሳሳይ ከጊኒ ጋር ጥቅምት 4 ሊደረግ የነበረ ቢሆንም በአንድ ቀን ተራዝሞ ወደ ጥቅምት 5 ቀን 2017 መሸጋገሩ ተመላክቷል፡፡
ይህ ጨዋታ የቦታ እና የሠዓት ለውጥ ሳይደረግበት አቢጃን በሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ምሸት 4 ሠዓት ላይ ይደረጋል ተብሏል፡፡