የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በከተማ ግብርና እንዲሰማሩ ጥሪ አቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

September 30, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተማ ግብርና እየተሳተፉ ያሉ የበለጠ እንዲያጠናክሩ እና ሌሎችም በዚህ የከተሞችን ዘላቂ ነገ በሚያረጋግጥ ተግባር እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የከተማ ግብርናን ሥራ የከተማ የአኗኗር ዘይቤ ስትራቴጂ አካል አድርገን ስናስፋፋ የማሻገር አቅሙ ላይ ጥርት ያለ መረዳት ይዘን ነበር ብለዋል።

የከተማ ግብርና የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከማጎልበቱ ባሻገር፤ የከተማ ምጣኔ ሃብትን እና የሥራ ፈጠራን ያሳድጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገር አቀፉን የምግብ ዋስትና ያጎለብታል፤ የከተማ ልማት ሥራን ይደግፋል፤ ተጠቃሚዎችን በቀጥታ ከአምራች የአካባቢው ገበሬዎች ጋርም ያገናኛል ነው ያሉት፡፡

ያለንን ውስን ቦታ እንደ የግድግዳ ላይ እና የደረጃ ግብርናን ብሎም ቁሶችን በድጋሚ በሚገባ በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ የአካባቢ ተጽዕኖን መቀነስ ችለናል ብለዋል።

በመላው ሀገራችን ይህ ሥራ የከተማ ግብርና የከተሞቻችንን ሁኔታ በመተለም እና ኢኮኖሚያችንን በማጠናከር ያለውን ጉልበት በማሳየት ከአሁኑ አመርቂ ውጤቶችን በማስገኘት ላይ ይገኛል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሁሉ ጥረቶቻቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ፤ ሌሎችም በዚህ በማደግ ላይ ባለ እና የከተሞችን ዘላቂ ነገ በሚያረጋግጥ ተግባር እንዲሳተፉ እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡