የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 75 የመኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች አስተላለፉ

By Meseret Awoke

September 29, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ክፍለ ከተማ ባለ 5 ወለል 75 የመኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች አስተላለፉ፡፡

በዊንጌትና ገብስ-ተራ የቀበሌ ቤቶችን በማፍረስ ለመኖር ምቹ የሆኑ 75 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው ባለ 5 ወለል ሁለት ሕንጻዎችን በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፋቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቶቹ ከቦታው ከተነሱ ነዋሪዎች በተጨማሪ ለልማት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለሚነሱ ዜጎች የሚተርፉ ሆነው መገንባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ልማቱ ነዋሪዎችን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት እና ምቹ በሆኑ የመኖሪያ አካባቢዎች የመኖር ዕድልን የሚፈጥር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡