Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ አረጋ ከበደ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የፍትሕ ተቋማት ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የፍትሕ ተቋማት ሠራተኞች የሕዝብ አገልጋይነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ፡፡

በባሕር ዳር እየተካሄደ በሚገኘው የአማራ ክልል የዳኝነትና ፍትሕ አካላት የትብብር ጥምረት መድረክ ላይ ርዕሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት÷ የሕዝባችን አንዱ መሰረታዊ ጥያቄ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ነው ፤ የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ትልቅ ርምጃ ነው።

የፍትሕ ተቋማቱ ትብብር ከምንጊዜውም በላይ በተግባር ላይ የተመሰረተና ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡

የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስም ሁሉም የፍትሕ ተቋማት ሠራተኞች የሕዝብ አገልጋይነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ÷በፍትሕ ተቋማት ላይ እምነት የማጣት ዝንባሌ እንዳይኖር እንዲህ ዓይነቱ ችግርን አውቆ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት በበኩላቸው፥ ተቋማቱ የተቀራረበ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ባለቤት ማድረግና የሕዝብን አመኔታ እንዲይዙ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የፍትሕ አካላት ሪፎርም በተሟላ ደረጃ እንዲተገበርም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

መሰል ምክክር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ጥሩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ናቸው፡፡

መድረኩ የዳኝትና የፍትሕ አካላት የየራሳቸውን ተቋማዊ ነጻነት ጠብቀው ከፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ አንጻር የሚያጋጥማቸውን የጋራ ተግዳሮት ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የመምከር ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።

በደሳለኝ ቢራራ

Exit mobile version