የሀገር ውስጥ ዜና

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ለውጥ እየተገኘ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By Shambel Mihret

September 28, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተከናወኑ በሚገኙ የግብርና ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየተገኘ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ባምባሲ ወረዳ አያንቱ ቀበሌ በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኘውን በቆሎ ሰብል በጎበኙበት ወቅት÷ በክልሉ የኩታ ገጠም የአስተራረስን ዘዴን በመጠቀም እየተከናወነ የሚገኘው የመኸር እርሻ ምርታማነትን ያሳድጋል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በምግብ ራስን ለመቻል አይነተኛ መሳሪያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአርሶ አደሩ በኩታ ገጠም የማረስ ልምድ እየተሻሻለ ስለመምጣቱም ጠቁመው፤ የኩታ ገጠም አስተራረስን በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች በማስፋፋት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኻልፋ በበኩላቸው÷ በተያዘው የምርት ዘመን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ማሳን በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩን የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነ ተግባርም በክልሉ ከ370 ሺህ በላይ ማሣ በኩታ ገጠም ለማረስ ታቅዶ 200 ሺህ ሄክታር ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑም በሁሉም የሰብል አይነቶች 45 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡