Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል – አቶ ሃይሉ አዱኛ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉን አቀፍ ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡

መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበሩትን የዘንድሮው ሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ አርሰዴ ኢሬቻን አስመልክቶ አቶ ሃይሉ አዱኛ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ ዋቃ (አምላክ) ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

እንዲሁም መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ”ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ገልጸው፤ በዓሉ ሰላምን፣ ይቅርታ፣አብሮነትና ወንድማማችነትን እንዲሁም የኦሮሞ እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንደሚከበር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ቂም፣ ጥላቻና በቀል በኢሬቻ በዓል ቦታ የላቸውም ያሉት ሃላፊው፥ በዓሉ የእርቅ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት መሆኑን አስረድተው፤ በዓሉ የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ መገናኛ ብዙሃን እሴቶቹን በሚገባ ተደራሽ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በየደረጃው ኮሚቴ ተዋቅሮ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

የመገናኛ ብዙሃን፣ የጸጥታ አካላት፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የበዓሉ ተሳታፊዎችና ሌሎች አካላት በዓሉ በስኬት እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሲምብሮ በበኩላቸው÷ የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የአብሮነት፣የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነና የይቅርታ በዓል መሆኑን አውስተዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የኢሬቻ በዓልን ምንነት ለማሳወቅና ለማስተማር እንዲሁም አከባበሩን ለመሰነድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በዓሉን ከማስተዋወቅ ባሻገር አሉታዊ ዘገባዎችን ማምከን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዓሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version