የሀገር ውስጥ ዜና

የጦር መሣሪያ እሽቅድድም፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት የሚሹ ናቸው – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

By Shambel Mihret

September 28, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር መሣሪያ እሽቅድድም፣ አስከፊ ድህነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የገጠሙ መሠናክሎች የተመድ እና አባል ሀገራቱን ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግ÷ ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት እና የባለብዙወገን ግንኙነት መርሆችን አክብራ የምትጓዝ መሆኗን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ተመድ በርካታ ፈተናዎች እያጋጠሙት መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ቀደመ የባለብዙ ወገን ግንኙነት መርሆች መመለስ እና አባል ሀገራቱም በመካከላቸው ያለውን የትብብር መንፈስ በማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ በሆነው የአረንጓዴ ዓሻራ ትግበራ የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ3 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በቀይ ባሕር እና ሕንድ ውቅያኖስ ያለው ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን በመሥራት እና እንደ አልሸባባ ያሉ አሸባሪ እና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመዋጋት ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

በሶማሊያ አሸባሪነትን በመዋጋት ረገድ ለሶማሊያ ሕዝብ ፅናት እና ዋጋ ለከፈሉ የቡሩንዲ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ ልጆች ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ውጭ ያሉ ኃይላት በቀጣናው ውጥረት ከመፍጠር እንዲታቀቡም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት በሶማሊያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና በቀጣናው የተሳሰረ ዕድገት እና ብልጽግና ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል።