የሀገር ውስጥ ዜና

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱን ሀገራት በጋራ የመበልፀግ ሕልም እውን የሚያደርግ ነው – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

By Shambel Mihret

September 28, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱን አገራት በጋራ የማደግ እና የመበልፀግ ሕልም እውን እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

አምባሳደር ታዬ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ማዕቀፉ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ሊገባ መቃረቡን ገልጸዋል።

ስምምነቱ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን የሚያሰፍን ነው ብለዋል።

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱን አገራት በጋራ የማደግ እና የመበልፀግ ሕልምን እውን የሚያደርግ ታሪካዊ ማዕቀፍ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራት ስምምነቱን በማፅደቅ ለማዕቀፉ ውጤታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ አምባሳደር ታዬ ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከኢትዮጵያ የኢነርጂ ኃይል የማግኘት ፍላጎትና በቀጣናው ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሻት የመነጨ ነው ብለዋል።

ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው ትስስርና ትብብርን የማጎልበት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል።