Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በ79ኛው የተመድ ጉባዔ ላይ ቁጣና ዛቻ የተቀላቀለበት ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም÷ዜጎች ወደ ቀያቸው እስካልተመለሱ ድረስ እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ የምትወስደው ሁለንተናዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ሃማስ እጅ ከሰጠ ጦርነቱ ወዲያውኑ ያቆማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ይሁን እንጂ እስራኤል ሂዝቦላህን በሊባኖስ የማሸነፍ ግዴታ አለባት ብለዋል፡፡

ከቀን በፊት ሃማስና ሂዝቦላህ በተኮሱት ሮኬት ሳቢያ በሰሜን እስራኤል 60 ሺህ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አስረድተዋል፡፡

“ሁሉም ነገር ማብቃት አለበት፤እስራኤል ዜጎቿ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እስካልተመለሱ ድረስ እረፍት የላትም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሰሜን እስራኤል እንደ ጥቅምት 7ቱ አይነት ዘግናኝ ጥቃት የሚፈጽም አሸባሪ ቡድን እንዲሰፍር አንፈቅድም ነው ያሉት ኔታንያሁ ባስተላለፉት ቁጣ አዘል መልዕክት፡፡

ሂዝቦላህ በሊባኖስ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በመመሸግ ሚሳኤልና ሮኬት ወደ እስራኤል እያስወነጨፈ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም ጦርነቱ የሊበኖስን ሕዝብ ምሽግ ካደረገው ሂዝቦላህ ጋር እንጂ ከሊባኖስ ሕዝብ ጋር እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

እስራኤል ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ሀገራቸው ስጋቷን የማስወገድ ሙሉ መብት እንዳላትም አንስተዋል፡፡

እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ እየወሰደች ባለው እርምጃ በሊባኖስ እስካሁን 700 በላይ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ኢራን በቀጥታ በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ ሀገራቸው ቀጥተኛና ከባድ አጸፋዊ እርምጃ ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

Exit mobile version