Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የሃይል ሥምሪት በጥንቃቄ መከናወን አለበት- አምበሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የሃይል ሥምሪት ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አሳሰቡ፡፡

አምባሳደር ታዬ ከዴንማርክ አቻቸው ላርስ ሎክ ራስምሰንና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሼህ ሻክቡት ናህያን አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ታዬ በውይይቱ ላይ ዴንማርክ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች እና ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ባላት ቁርጠኝነት ዙሪያም ገለጻ አድርገዋል።

በተያያዘ አምባሳደር ታዬ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሼህ ሻክቡት ናህያን አል ናህያን ጋር በሁለትዮሽና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ መክረዋል።

ሶማሊያን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት አምባሳደር ታዬ የቀጣናው ሀገራት ዋጋ የከፈሉበትና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ወጪ ያወጣበት የሶማሊያ ደህንነት እንዲቀጥል ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የሃይል ሥምሪት ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ውይይቱ በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተመድ ጉባዔ ጎን ለጎን መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version