አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዘመናዊ ከተማ ግንባታና በቱሪዝም መሠረተ-ልማት ተጨባጭ ለውጥ እያሳየች መሆኑን የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ተናገሩ።
በ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ላይ አዲስ አበባ የተገኙ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች÷ኢትዮጵያ አስገራሚ ባህል፣ አንድነትና ሕብረ-ብሔራዊነትያላት ሀገር አንደሆነች መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመሠረተ-ልማት፣ በቱሪስት መዳረሻ ልማት፣ በዘመናዊ ከተማ ግንባታ፣ ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎችና መስተንግዶ በማቅረብ ተጨባጭ ለውጥ ማሳየቷንም አንስተዋል።
የሚታየው ለውጥም ኢትዮጵያ ያላት ድንቅ ባህልና እሴት በስፋት እንዲጎበኝ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጎብኝዎቹ ተናግረዋል።
ከአሥር ዓመት በፊት ኢትዮጵያን የጎበኙት ስዊዲናዊው ሌናርት ካርልሰን በ2017 ዓ.ም. ወደ ሀገሪቱ ሲመጡ ዘርፈ-ብዙ አስገራሚ ለውጥ ማየታቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ከዘመናዊ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን የዘመናዊ ህንፃ ግንባታ፣ የመንገድ መሠረተ-ልማትና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አስደናቂ ለውጥ ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
ከተማዋ የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ በዓለም መድረክ ተወዳዳሪነቷን የበለጠ እንደሚያሳድግ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ለ26 ዓመታት የኖሩት እንግሊዛዊው አንቶኒ ኮውቲያን በበኩላቸው÷ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የተደረገው ፈጣን ለውጥ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
በሀገሪቱ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች የምጣኔ ኃብት እድገትና ልማትን ማምጣት የሚያስችሉ እንደሆኑ ምልከታቸውን አጋርተዋል።
ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የሚጎበኙት ቤልጄማዊቷ ኤልሲ ዲሀኖስቻተር÷ ኢትዮጵያ ባላት ድንቅ ባህልና እሴት መጎብኘት ያለባት ሀገር እንደሆነች ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለተመሳሳይ ዓላማና ግብ በአንድነት መቆም በኢትዮጵያ እንዲሁም በአዲስ አበባ ለሚታዩ ተጨባጭ ለውጦች ምክንያት ናቸው የሚል አስተያየት የሰጠው ደግሞ ጃማይካዊው ኃይሌ ዲያን ነው።
ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪስት መሠረተ-ልማትና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለመጎብኘት መዳረሻቸው እያደረጓት እንደሆነም ጠቁሟል።