አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በትግራይ ክልል ዓዲግራት ከተማ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ÷ በዓሉን ስናከብር እርስ በርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዘላቂ ሰላም ለትግራይ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም የትግራይ ሕዝብን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አፅበሃ ገ/እግዚአብሄር (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
የመስቀል በዓል እሴቶች ተጠብቀው አሁን ላይ እንዲደርሱ ላደረጉ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ለክልሉ ሕዝብ ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።