Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኮደርስ ሥልጠና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ ሚና አለው -አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን የኮደርስ ሥልጠና በንቃት እንዲወስዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ስልጠናው “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

አቶ ጥላሁን ስልጠናውን አስመልክተው ለኢዜአ እንዳሉት÷ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክኅሎት ያላቸው ወጣቶችን ከማፍራት አንጻር ሥልጠናው የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው።

በክልላቸውም ይህን የ5 ሚሊየን ኮደርስ ፕሮግራም የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም በርካቶች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት የወሰዱ መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡

የኮደርስ ሥልጠና በተለይ ወጣቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ÷ዕድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version