አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘላቂነት የሀገሪቱን የምግብ ሥርዓት ለመቀየር በግብርና ምርት አቅርቦት ሰንሰለት ማሻሻያና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ ትብብሮችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በጣሊያን ሳራኩዛ እየተካሄደ ከሚገኘው የቡድን ሰባት ሀገራት የግብርና ፎረም ጎንለጎን ከጣሊያን እና ደቡብ አፍሪካ የግብርና ሚኒስትሮች እንዲሁም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (ፋኦ) ረዳት ዋና ዳይሬክተር ጋር በግብርናው ዘርፍ በሚደረጉ ትብብሮች ላይ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት÷ ሀገራቱ ካላቸው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አኳያ በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሰፊ ዕድል መኖሩን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የሌማት ትሩፋት እና የስንዴ እርሻ ልማት ተሞክሮ ማካፈላቸውን በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በእንስሳት ጤና፣ በግብርና ምርቶች የንግድ ልውውጥና በግብርና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በቀጣይ በሚደረጉ የዘርፉ ትብብሮች ላይ በቴክኒካል ቡድን ደረጃ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባቢያ ስምምነቶችን ለመፈራረምም መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከፋኦ ረዳት ዋና ዳይሬክተር ቫሌሪ ጉኔሪ ጋር ባደረጉት ውይይት ድርጅቱ በኢትዮጵያ በዘላቂነት የምግብ ሥርዓትን ለመቀየር በግብርና ምርት አቅርቦት ሰንሰለት ማሻሻያ፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በስልጠና እና አቅም ግንባታ ላይ ትብብሮችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡