አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል ደመራ በዓል በሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓትና ድምቀት ተከብሮ እንዲውል ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቀረበች፡፡
ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል ዐደባባይ የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የምሥጋና መግለጫ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
በቀረበው መልዕክትም ሕዝበ-ክርስቲያኑ ዝናብና ቁር ሳይበግረው በጽናትና ፍጹም በሆነ መንፈሳዊነት በዓሉን በድምቀት ማክበሩን የገለጸችው ቤተ-ክርስቲያኗ÷ ተረኛው ደብር፣ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በበዓሉ ላይ መንፈሳዊ ትርኢት ሲያቀርቡ ለነበሩት ሁሉ ላሳዩት ጨዋነት የተሞላው መታዘዝ አመስግናለች፡፡
ሕዝበ-ክርስቲያኑ ወደ መስቀል ዐደባባይ በሚጓዝበት ወቅት ፍጹም ጨዋነትና መንፈሳዊነትን በተላበሰ መልኩ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት ትብብር በማድረግ ራሱም ጸጥታ አስከባሪና ተባባሪ በመሆን ያሳየው ድንቅ ተግባር የሚደነቅ ነው ብላለች፡፡
ምዕመኑ ቤተ-ክርስቲያኗ ከበዓሉ አስቀድማ ያስተላለፈቻቸውን የጥንቃቄ መልዕክቶች በሚገባ በመፈጸም ታዛዥነቱን በማስመስከሩም አመስግናለች፡፡
እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የፖሊስ፣ የደኅንነት እና የጸጥታ አካላት ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው ቤተ-ክርስቲያኗ ምሥጋና አቅርባለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርም በዓሉ ደማቅ በሆነ መልኩ እንዲከበር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላትን ጨምሮ ቤተ-ክርስቲያኗ ያቀረበችለትን ጥያቄ ሁሉ በቅንነት ምላሽ በመስጠት ላደረገው ትብብር ተመስግኗል፡፡
ይህ ዓይነቱ መተጋገዝና የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል መባሉን ከቤተ-ክርስቲያኗ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በጠቅላይ ቤተ-ክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁ ኮሚቴዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር በጥምረት ላከናወኑት ስኬታማ ሥራ ቤተ-ክርስቲያኗ አመሠግናለች፡፡