የሀገር ውስጥ ዜና

የብሪክስ ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲሰፍን ጉልህ ሚና እንደሚጠበቅበት ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

September 27, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲሰፍን በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ጉልህ ሚና ይጠበቅበታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ  አስገነዘቡ፡፡

በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደር ታዬ ባደረጉት ንግግር በዓለም አቀፍ ተቋማት አሥተዳደር እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ፍትሐዊ ውክልና እና ተሰሚነት እንዲሰፍን በሚደረገው የማሻሻያ ጥረት የብሪክስ ማዕቀፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የባለብዙወገን ዓለም አቀፍ ተቋማቱ አሳታፊ እና ጠንካራ እንዲሆኑ የተጀመሩ የማሻሻያ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ማሻሻያው ቅድሚያ ለአፍሪካ ውክልና መስጠት እንደሚገባው እና ታማኝ እና ፍትሐዊ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ ኢትዮጵያ የምታራምደው አቋም የአፍሪካን አቋም ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለአፍሪካ ሕጋዊ ጥያቄ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ምላሽ ሊሰጠው እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

ውክልናው መልከዓ-ምድርን፣ የብሪክስን የጋራ ዕሴቶች እና በብሪክስ ማዕቀፍ አባል ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እና የተመድን ቻርተር ባማከል መልኩ መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እነዚህ መርሆች ብሪክስ በዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ እና ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር የሚጫወተውን ሚና የበለጠ ያጠናክሩለታል ነው ያሉት፡፡