አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት በመላው ኢትዮጵያ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበሮ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት እና ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በዕቅድ እየተመራ ተጋላጭ ቦታዎችንና አካባቢዎችን ለይቶ በቅድመ መከላከል ሥራው ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የሰው ኃይል በማሰማራት ከህዝቡ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከወጣቶች ጋር ተባብሮ በመስራቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በዓሉ በድምቀት ተከብሮ መቻሉን አስታውቋል፡፡
በዓሉ በድመቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው ህዝብ እንዲሁም ለሀይማኖት አባቶች፣ ለበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ ለወጣቶች እና በተለይ የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ የተወጡት የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎችንም ማመስገኑን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር በቀጣይ በሚከበሩበት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት ላይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡