አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል በዓል እሴቱን ጠብቆ የሀገር ሃብት ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስገነዘቡ።
አገልግሎቱ የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በመላዉ ኢትዮጵያ የደመራ እና የመስቀል በዓል ጥንታዊነቱን ይዞ የቀጠለ የዐደባባይ በዓል ነው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸዉ ቅርሶች መካከል አንዱ መሆኑንም አስታውሷል።
የዐደባባይ በዓላቶቻችን የአብሮነት እሴቶቻችንን የሚያጎሉ፣ የብዝኃነታችን ጌጥነት ማሳያዎች ከመሆን ባሻገር የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ሀብቶቻችን እየሆኑ መጥተዋል በማለትም ገልጿል።
የመስቀል በዓልን ስናከብር የዓለም የቱሪዝም ቀንን ጭምር እያከበርን ነው ያለው አገልግሎቱ፤ እንደ ዓለም ቱሪዝም ድርጅት አባልነታችንና በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን እንዳስመዘገበ ሀገር ኢትዮጵያ ቀኑን በልዩ ልዩ ኹነቶች ታከብራለች ሲል ገልጿል።
የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበዉ የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴትነቱም በተጨማሪ የቱሪዝም ትሩፋት በመሆኑ በዓሉ እሴቱን ጠብቆ የሀገር ሃብት ሆኖ ደምቆ እንዲቀጥል ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝቧል።
በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ የዐደባባይ በዓላቶችንና የዓለም ቱሪዝም ቀንን ስናከብር በዘመናችንም ለቅርስነት የሚበቁ ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወንን ነው ሲል ገልጿል።
ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቁ የመዳረሻ ቦታዎች መታደሳቸውን፣ መልማታቸውን ገልጾ፤ አሁንም በመልማት ላይ እንደሆኑ አመልክቷል።
እነዚህ ሥራዎቻችን ለቀጣዩ ትውልድ የኩራት ምንጭ የሚሆኑ ቅርሶች ጭምር ናቸው ያለው አገልግሎቱ፤ ሀገራችንን፣ ታሪካችንን፣ ባህላችንን ማወቅና ማስተዋወቅ ለመጠበቅ ሚናዉ ጉልህ ነውና ከሁላችንም ይጠበቃል ብሏል በመልዕክቱ።