የሀገር ውስጥ ዜና

የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት ይከበራል

By Shambel Mihret

September 26, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 ዓ.ም መስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት ይከበራል።

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ሚኒስትሮችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቱሪስቶች በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ሰዓትም በመስቀል አደባባይ የተገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ወረብ እያቀረቡ ሲሆን፤ ላለፈው አንድ ዓመት ዝግጅት ሲያደርግ በቆየው የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መሪነት የመስቀል ደመራ ስነ ስርዓት ይከናወናል።

በበዓሉ ላይ በስምንት ቋንቋዎች የተዘጋጁ መዝሙሮች የሚቀርቡ ሲሆን፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶችም የተለያዩ መዝሙሮችን እና ትርዒቶችን እንደሚያቀርቡ ተነግሯል።

በመሳፍንት እያዩ