Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመስቀል በዓል የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ እያገዘ ነው – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል በዓል የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ በማገዝ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የ2017 ዓ.ም የመስቀልን በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገፅታ እንዳለው ገልጸዋል።

ተራርቀዉ የሠነበቱ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ቤተሰባዊና ማህበረሰባዊ ትስስሮች የሚታደሱበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን በማጠናከር የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ በማገዝ የበኩሉን ሚና እያበረከተ ይገኛል ሲሉም ጠቁመዋል።

የመስቀል በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀገር ደረጃ መስከረም 17 ቀን ከሚከበረዉ በዓል ቀደም ብሎ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መከበር ይጀምራል፣ በደማቅ የበዓል ድባብ ታጅቦም ለቀናት እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡

በዚህም በክልሉ የበዓሉ ስነ ስርዓቶች በተለያየ መልኩ ተጀምረዋል፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ወላጆችን እና ቤተሰቦችን ጥያቃ ከተለያዩ ከተሞች ወደ ገጠር የሚጓዙ ታዳሚዎች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት አጎናፅፈዉታል ሲሉም ርዕሰ መስተዳደሩ የበዓሉን ድባብ ገልጸውታል።

የዘንድሮዉን የመስቀል በዓል ስናከብር ለሠላምና ለአብሮነት መሠረት የሆኑ እሴቶችን በማጠናከር፣ ለጋራ ለዉጥና ዕድገት በጋራ ለመትጋት ቃላችንን እያደስን መሆን ይኖርበታል ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version