የሀገር ውስጥ ዜና

መስቀል በአስቸጋሪ፣ በፈታኝና በድንግዝግዝ ውስጥ ሆኖ ነገን የማየት ተምሳሌት ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Shambel Mihret

September 26, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መስቀል በአስቸጋሪ፣ በፈታኝና በድንግዝግዝ ውስጥ ሆኖ ነገን የማየት ተምሳሌት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመስቀል በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ የመስቀል በዓል ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በኢትዮጵያውያን የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።

አከባበሩ ኅብራዊ ነው፣ የየአካባቢው ቀለም ይጨመርበታል፣ የሚከበረው ግን በተመሳሳይ ወቅት ነው፣ ከግላዊ ይልቅ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

መስቀል ነባር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ያሳያል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በብዙ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላት በመስከረም ወር፣ ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዘው መከበራቸው ጥንታዊ ማኅበራዊ ትሥሥራችንን ሳያመለክት አይቀርም ብለዋል፡፡

መስቀል በአስቸጋሪ፣ በፈታኝና በድንግዝግዝ ውስጥ ሆኖ ነገን የማየት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ንግስት ዕሌኒ በነበረችበት ዘመን መስቀሉ ተቀብሮ እንደነበር አስታውሰው እርሷም ከእምነት በቀር ዐቅም አልነበራትም ብለዋል፡፡

አንድ ቀን መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣትና ታሪኩን ለመቀየር ታስብ ነበር፣ ለዚህ ተምኔቷ ስትል ከማትፈልገው ሰው ጋር ኖረች፣ ደስ የማይላትን ሕይወት በትግልና በትጋት አለፈች ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተስፋዋን ቆስጠንጢኖስን ወልዳ አሳደገች፣ በታሪክ አልቆዘመችም፣ በነባራዊው ሁኔታ ተስፋ አልቆረጠችም፣ አይቻልምን ሳትቀበል፣ ከባድ ነውን ሳታምን ጉልበቷን በዓላማዋ ላይ አፈሰሰች፣ ትኩረቷን በሕልሟ ላይ አደረገች ብለዋል።

በመጨረሻም የማይቻለውን ቻለች፣ የማይሞከረውን አሳካች፣ የተቀበረውን የክርስቶስ መስቀል አወጣች፣ አንድ ብቻዋን የነበረች ሴት ዓለምን አስከተለች፣ የመስቀሉን ታሪክ ቀየረች ብለዋል፡፡

የሚያዳክሙንን አንስማ፣ ተስፋ ለሚያስቆርጡን ልብ አንስጥ፣ በዙሪያችን ችግሮች አንወሰድ፣ በፈተናዎች ብዛት አንገረም፣ ትኩረታችንን በሕልማችን ላይ ብቻ እናድርግ፣ በመጨረሻ የድል ደመራውን መደመር የእኛ ይሆናል ነው ያሉት፡፡