አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መሬት በምደባ ወስደው ለዓመታት ሳያለሙ በቆዩ አካላት ላይ አስተማሪ ርምጃ እንደሚወሰድ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በመንግሥት እና በግል ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልጸዋል፡፡
የአብዛኛው ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መሻሻል ማሳየቱን እና አንዳንድ የመንግሥት እና የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደግሞ አዝጋሚ መሆኑንም በጉብኝታቸው መመልከታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በቀጣይ ለመቅረፍ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
በግል ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት በምደባ ወስደው ለዓመታት ሳያለሙ በቆዩ አካላት ላይም አስተማሪ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡