አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ከከተማ ርቀው በገጠር ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለጸ።
የዓለም ባንክ ከፍተኛ ሃላፊዎች በጤና ሚኒስቴር እየተተገበሩ የሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡
ሃላፊዎቹ በቢሾፍቱ የሚገኘውን የጨለለቃ ጤና ጣቢያን በጎበኙበት ወቅት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ነጻነት ወርቅነህ (ፕ/ር)÷ ጤና ጣቢያው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ጤና ጣቢያው ሁለት ጤና ኬላዎችን የሚደግፍ በመሆኑ በገጠር ለሚገኙ አርሶ አደሮች አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረጉ በተጨማሪ ለቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎትን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የሥራ ሃላፊዎቹ በጤና ጣቢያው እየተሰጠ የሚገኘውን የማዋለድ እና የድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት እንደጎበኙም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የዓለም ባንክ ልኡካንም አባላት÷ በጤና ጣቢያው እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት ከመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት መስጫ ከሚጠበቀው በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተመለከቱት አገልግሎት በሁሉም ጤና ጣቢያዎች የሚገኝ አለመሆኑን እንደሚረዱ እና በተለይም ከከተማ ርቀው የሚገኙ ሌሎች ጤና ጣቢያዎች ተመሳሳይ አገልግሎት በመስጠት በርቀት ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚኒስቴሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
ልዑኩ እየተገነባ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ የጥራት ላብራቶሪ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃም ጎብኝተዋል፡፡