አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ እየተሳተፈች ነው።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በመድረኩ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ይገኙበታል።
ከጉባዔው ጎን ለጎን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፣ ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ፣ ከተመድ የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር በሁለትዮሽና በሌሎች ትኩረት በሚሹ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ራምዳን ሞሀመድ አብዱላህ እና ከአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አታፍ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
በተጨማሪም የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነውና ከ140 በላይ የሀገር መሪዎች የተሳተፉበት የመጪው ጊዜ ጉባዔ ላይ አምባሳደር ባደረጉት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጥ መልኩ እንዲከናወን መጠየቃቸው ይታወሳል።