አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩታ-ገጠም እርሻ ጠቀሜታን በመረዳት የአርሶ-አደሩ ተሳትፎ እያደገ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጸጋዬ ተሰማ ገለጹ፡፡
በ2016/2017 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እስከ አሁን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር የሚልቀው መሳካቱንም ገልጸዋል፡፡
በጸጥታ ችግር የቆዩ አካባቢዎችም አሁን ላይ በተገኘው ሰላም አበረታች የግብርና ሥራ እያከናወኑ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የክልሉ አርሶ አደሮች የኩታ-ገጠም እርሻ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታን ተረድተው እያደረጉት ያለው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለአብነትም እስከ አሁን በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 189 ሺህ 244 ሔክታሩ በኩታ-ገጠም እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ ከ45 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡