የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም ለጦርነት የምታባክነውን ሀብት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ማዋል አለባት – ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ

By Feven Bishaw

September 25, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ለጦርነት የምታባክነውን ሀብት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ማዋል አለባት ሲሉ የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊስ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ገለጹ።

በኒውዮርክ እየተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) 79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ መካሄዱን እንደቀጠለ ነው።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ፤ የዓለም መሪዎች ሰላም በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እየከፋ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የዓለም መሪዎችን ሊያሳስባቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ ከፍተኛ አውሎ ንፋስ፣ ድርቅ እና ጎርፍ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለውና ውሽንፍር የቀላቀለ ሀይለኛ ዝናብ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት እየተደጋገመ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰላም በመፍጠር ለጦርንት እየባከነ ያለውን ሀብት የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ የተመድ ቻርተር ሰፊ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም ደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ ከፀጥታው ምክር ቤት መገለላቸው ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰው፤ ለማሻሻያው መስራት ይገባል ብለዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ በመጣው የግጭት ሁኔታ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምስራቅ እየሰፋ የመጣው ጦርነት መቆም እንዳለበት በማሳሰብ በተለይም እስራኤል እና ሂዝቦላህ ግጭቱ ሳይባባስ የመቋጨት ሰፊ እድል አላቸው ብለዋል፡፡

የለየለት ጦርነት የትኛውንም ሀገር ተጠቃሚ አያደርግም ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን፤ ሰላማዊ ግንኙነቶች ውጤት እንደሚያስገኙ ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው በጋዛ በሚካሄደው ጦርነት ንጹሐን ሰለባ መሆናቸውን አንስተው፤ ግጭቱ በሰለማዊ መንገድ ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የዓለም መሪዎች ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ ተመድ እጠብቀዋለው የሚለውን ሰብዓዊ መብት በጋዛ መፈጸም አልቻለም፤ ህጻናትን ጨምሮ ንፁሃን እያለቁ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡