Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም 112 የመስኖ ግድቦች ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች 112 የመስኖ ግድቦች ተገንብተው ለአርሶ አደሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ኑረዲን አሳሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ሚናው ከፍተኛ ነው።

በዚህ ረገድ ፕሮግራሙ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ለአርሶ አደሮች የመስኖ ግድቦችን በመገንባት በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉን አንስተዋል።

ፕሮግራሙ በሰባት ክልሎች በ32 ዞኖች፣ 103 ወረዳዎችና 154 ቀበሌዎች ሲተገበር መቆየቱን ነው የተናገሩት።

በዚህም 112 የመስኖ ግድቦችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የአርሶ አደሮችን ምርት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሮች በአነስተኛ የመስኖ ግድቦቹ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ጨምሮ ስንዴና ሌሎች ሰብሎችን እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) በበኩላቸው፥ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የአርሶ አደሮችን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ መሰል ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአነስተኛ መስኖ ግድቦቹ ግንባታ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) እና ሌሎች አጋር አካላት በተገኘ ድጋፍና ብድር መከናወኑ ተመላክቷል።

 

Exit mobile version