Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለደመራና መስቀል በዓል መስቀል ዐደባባይን የማጽዳት ሥራ ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የመስቀል ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ በመስቀል ዐደባባይ የፅዳት ሥራ አከናወነ፡፡

 በጽዳት ሥራው ላይም የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች እና ምዕመናን ተሳትፈዋል፡፡

 የከተማ አሥተዳደሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በዚሁ ወቅት÷ የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖትነቱ ባሻገር የኢትዮጵያውያን መገለጫና የጋራ ሀብታችን ነው ብለዋል፡፡

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው÷ የመስቀል በዓልን የምናከብረው በመስቀሉ የተሠራልንን ድንቅ ተዓምር ለመግለጽ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

 ቤተክርስቲያኗ በመስቀሉ የምታስተምረው ሰላምን መሆኑን በመግለጽ÷ ይህንን ሰላም በትብብር ማፅናት የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

 ከቤተክርስቲያኗ ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ የተገኙትን ሁሉም በቤተክርስቲያኗ ስም አመስግነዋል።

 የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የመስቀል በዓል ከሃይማኖት መገለጫነቱ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ÷ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 በዓሉ በሰላም ሲከበር ኢትዮጵያውያንን በዓለም ዐደባባይ በማንገስ አንድነታችንን ያጠናክራልና በልዩ ትኩረት ልናከብረው ይገባል ምክንያቱም አንዳችን ያለአንዳችን ድምቀት የለንምና ብለዋል።

 የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች እና ምዕመናን በበኩላቸው መስቀል የአብሮነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዓሉን በትብብርና በአንድነት በማክበር የነበረውን ኢትዮጵያዊ ትስስራችንን እናስቀጥላለን ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version